ስለ ፎረሙ

የቤተሰብ ቢዝነሶች አስፈላጊነት

የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሚጫወተው ጉልህ ሚና ላይ የቤተሰብ ቢዝነሶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ከሞላ ጎደል በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ይኸውም ለአብነት ለመጥቀስ ያህል በአስመጪና ላኪነት ፣ በኢንዱስትሪ ፣ በትምህርት፣ በግብርና ፣ በጤና ፣ በፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦትና ስርጭት ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ፣ በግንባታና ሌሎች እዚህ ላይ ባልተጠቀሱ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የቤተሰብ ቢዝነስ አስተዋጽኦ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በዚህም ምክንያት የቤተሰብ ቢዝነሶች ቀጣይነትን ማረጋገጥ ማለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሀገርን ኢኮኖሚ ማሻሻል ፣ የስራ ዕድሎችን መፍጠር ፣ ሀገርን ወደፊት የሚያራምዱና በየዘርፋቸው ፈጣን ለውጥ ማስመዝገብ የሚችሉ ተቋማትን መገንባት ነው።

በአደጉት ሀገራት የሚታዩት ተሞክሮዎችም ይህንን በግልጽ የሚያሳዩና የሚደግፉ ናቸው። መቀመጫቸውን በምዕራቡ ዓለም ያደረጉና አለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ያላቸው ፣ ዛሬ በየቤቶቻችን ምርቶቻቸውን በመደበኛነት የምንጠቀምባቸው ተቋማት አብዛኞቹ ከቤተሰብ ቢዝነስ ጎራ የሚመደቡና ለረጅም ዓመት በዘርፋቸው ላይ በመቆየት ፣ ምርቶቻቸውን ያለማቋረጥ በማሻሻልና ተወዳዳሪነታቸውን በአለም አቀፋዊ ደረጃ በማረጋገጥ የሀገራቸው ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትልቅ አሻራ ያሳረፉ ቢዝነሶች ናቸው።

የቤተሰብ ቢዝነሶች በኢትዮጵያ

ይህንን ተመልክተን ወደ ሀገራችን ስንመለስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቤተሰብ ቢዝነሶች በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት የአቅማቸውን ያህል ሲያድጉ አይስተዋልም። ከእነዚህም ተግዳሮቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የአመራር ክፍተቶች ፣ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ያለመቻል ፣ ቀጣዩ ትውልድ በተተኪነት [የቢዝነስ ባለቤቶቹ ልጆች ወይም የቅርብ ዘመዶች] ቢዝነሱን ከመሰረቱት [ከእናት ፣ ከአባት/ ከእህት ፣ ከወንድም] ተረክቦ ማስቀጠል አለመቻል ናቸው።የኢትዮጵያ የቤተሰብ የንግድ ስራ ባለቤቶች መድረክ

ከላይ የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች በትብብር ለመፍታት እንዲያስችል ፤ ኤች ኤስ ቲ ኮንሰልቲንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፤ በዓይነቱ ልዩ የሆነ “የኢትዮጵያ የቤተሰብ የንግድ ስራ ባለቤቶች መድረክ” ተብሎ የሚጠራ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል። መድረኩ ከቤተሰብ ቢዝነስ ባለቤቶች ፣ የንግድ ዘርፍ ማህበራት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና በጉዳዩ ላይ በቀጥታ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር በትብብር እንዲካሄድ ታቅዶ የተቋቋመ ነው።

በቀጣይም ኤች ኤስ ቲ በዓመት አንድ ጊዜ መድረኩን የሚያዘጋጅ ሲሆን የማያቋርጥ ድጋፍ መስጠት እንዲያስችል የመድረኩ አባል ለሚሆኑ የቤተሰብ ቢዝነሶች ዋና በሚባሉና ለእድገታቸው ምሰሶ በሆኑ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ወርክሾፖች የሚዘጋጁ ሲሆን በየጊዜውም ተመሳሳይነት ባላቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች እየተዘጋጁ የሚቀርቡና የሚሰራጩ ይሆናል።