ሰርቬይ


የሀገር ኢኮኖሚዎች በፍላጎት አይገነቡም። እድገታቸው ቀጣይነት ባለውና አስተማማኝ በሆነ መልኩ የሚያንቀሳቅስ ሞተር መኖር አለበት ፤ ይህም ’የግል ዘርፍ’ [Private Sector] ነው። መንግስት ብዙ የኢኮኖሚ እንቅሳቃሴዎች ውስጥ በቀጥታ ገብቶ በሚሳተፍበት ጠንካራ ኢኮኖሚዎች ውስጥ እንኳን የግል ዘርፉ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው። አንድ ህብረተሰብ የትናንሽ ማህበረሰቦች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን የግሉ ዘርፍ ትልቁ ክፍል በቤተሰብ ንግዶች የተዋቀረ ነው።

ባለፉት ክፍለ ዘመናት ባደጉት ሀገራት ውስጥ የቤተሰብ ቢዝነስ የሀገራቸውን ኢኮኖሚ አቅጣጫ በመቅረጽ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና መመልከት ይቻላል። ከመስራቾቻቸው እና ከተፈጠሩበት የኢኮኖሚ አውድ በላይ የመቆየት አቅማቸውንም አረጋግጠዋል። የበለጸጉ ሀገራት ኢኮኖሚ ምንም እንኳን በኮርፖሬሽን መልክ የሚመሩ ድርጅቶች ተጽዕኖ ያለበት ቢመስልም አመሰራረታቸው የቤተሰብ ቢዝነስ እንደነበረና ፣ ውስጣዊ አስተዳደራቸው ትውልድን የተሻገረ የቤተሰብ ቢዝነስ አሻራ እንዳረፈባቸው ማንነታቸውን በጥልቀት ስንመረምር እናገኘዋለን።

በአለም አቀፍ ደረጃ ባለው ስታቲስቲክስ መሰረት ያደጉት ሀገራት በቤተሰብ ቢዝነሶች ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ከዘመን ዘመን ተሸጋግረው ሲሰሩ እናያለን ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ግን በብዙ ምክንያቶች ሊባል በሚችል መልኩ ፤ የቤተሰብ ቢዝነሶች ዕድሜያቸው ከመጀመሪያዎቹ መስራቾቻቸው አያልፍም። ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ በመፍጠር ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ እና ሚና በቢዝነስ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንኳን ትኩረት አልተሰጠውም። እንዲሁ ማንም ሳያስተውላቸውና ተገቢውን ትኩረት ሳያገኙ ይፈጠራሉ ይሞታሉ። በየቦታው በመገኘታቸው የተፈጥሮ ክስተቶች እንደሆኑ አድርገን ሳንቆጥራቸውም አንቀርም። ታሪካቸውን ፤ ጠቀሜታቸውንና ፈተናዎቻቸውን በአፅንኦት የሚከታተል የለም። ትንሽም ሆነ ምንም ሊባል በሚችል ደራጃ በስራ ፈጠራና በጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት [GDP] ላይ ያላቸውን አስተዋጾ በተመለከተ የተደረጉ ጥናቶች የሉም።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የኢትዮጵያ የቤተሰብ ንግድ ስራ መድረክ የተመሰርተ ሲሆን ፤ የቤተሰብ ቢዝነሶች ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ለኢኮኖሚው የሚያበረክቱትን አስተዋጾ የሚያሳዩ ጥናቶችን በማዘጋጀት እድገታቸውን የሚደግፉ ፤ ዘመናትን እንዲሻገሩና ሙያዊ በሆነ መልኩ መተዳደር የሚያስችላቸውን ስርዓቶች ለመዘርጋት ይሰራል። መድረኩ ከላይ የተገለጹትን ወሳኝ ጉዳዮች ዋና አጀንዳው በማድረግ ፤ የኢትዮጵያ ቤተሰብ ቢዝነሶች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የቅድመ-ምክክር መድረክ በመጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም አካሂዷል። ፎረሙ ከጥቂት ወራት በኋላ በይፋ ለመጀመር በማዘጋጀት ላይ ባለው መድረክ ላይ የሚቀርብና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቤተሰብ ቢዝነሶች ስለሚያጋጥሟቸው ችግሮች እና ለእድገታቸው የሚያስፈልጋቸው ድጋፎች ላይ የተመሰረተ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህ የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቤተሰብ ቢዝነሶችን ለማገዝ በየአመቱ የሚካሄድ ይሆናል። የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቤተሰብ ቢዝነሶች በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ስላላቸው አዎንታዊ ተፅዕኖ ለማወቅና እድገታቸውን ለማስቀጠል የሚያስችል ትክክለኛ መሰረት ለመጣል ትልቅ አስተዋጾ ይኖረዋል። ስለዚህ የእርሶም ኩባንያ በቤተሰብ ቢዝነስ የሚመደብ ስለሆነና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያደረገ ያለውን አስተዋጾ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ የዳሰሳ ጥናት ተሳታፊ እንዲሆኑና በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የቤተሰብ ቢዝነሶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ አሻራዎትን እንዲያኖሩ ጋብዘነዎታል። ለተጨማሪ ጥያቄዎች በ info@hst-et.com ላይ በመጻፍ ወይም በ0913851505 ሊያገኙን ይችላሉ።